የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላብራቶሪ በይፋ ስራ ጀመረ፡፡


Modified Date :2020-06-26
1_slott.jpg

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላብራቶሪ በይፋ ስራ ጀመረ፡፡ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላብራቶሪን በይፋ ስራ የማስጀመር ስነስርዓት ዛሬ ሰኔ 19/2012 ተካሂዷል፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላብራቶሪን በይፋ ስራ የማስጀመር ስነስርዓት ዛሬ ሰኔ 19/2012 ተካሂዷል፡፡ ላብራቶሪዉን የኢፌዲሪ ጤና ሚ/ር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በክብር እንግድነት ስራ ያስጀመሩት ሲሆን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንግስቱ በቀለ፣ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ አዲሱ ከበደ፣ የአምቦ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አቶ ሳህሉ ድርብሳ ፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በስነስርዓቱ ላይ ታድመዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታደሰ ቀነዓ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በሽታዉ ሊያመጣዉ የሚችለዉን የጤና፣ የህይወትና ማህበራዊ ቀዉስ በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲዉ እየተረባረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ስለበሽታዉ ግንዛቤ ኖሮት መከላከል እንዲችል ብዙ ስራዎች መሰራታቸዉንና አሁንም እየተሰሩ መሆናቸዉን ዶ/ር ታደሰ አስረድተዋል፡፡ በዚህም በምዕራብ ሸዋና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ስር በሚገኙ ትናንሽና መካከለኛ ከተሞች በመገኘት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸዉን፣ በርካታ በራሪ የማስተማሪያ ወረቀቶች መሰራጨታቸዉን፣ የዩኒቨርሲቲዉ ካምፓሶች በሚገኙባቸዉ አምቦ፣ ጉደርና ወሊሶ ከተሞች የኢኮኖሚ ችግር ለገጠማቸዉ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብ ግብኣቶችና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ 

 በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲዉ የፋርማሲ ት/ክፍል የእጅ ማጽጃ ፈሳሽ ( Sanitizer) ዓለም አቀፍ ደረጃዉን በጠበቀ መልኩ እየተመረተ ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተሰራጨ እንደሚገኝ አክለዉ ተናግረዋል፡፡ ለጉደር ሆስፒታል የኮሮና መታከሚያ ማዕከልም ከመቋቋሚያዉ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዉ በተለየ መልኩ ድጋፍ እያደረገለት እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ስራዉን የጀመረዉ ላብራቶሪ ወደ 10 ሚሊየን ብር ገደማ ወጪ ተደርጎበት የተደረጃ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ከሰራ በቀን አስከ አንድ ሺህ ናሙናዎችን መመርምር የሚችል መሆኑንና ይህንንም ለማደራጀት የኢፌዲሪ ጤና ሚ/ር፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ፣ የኢትዮጵያ የህ/ብ ጤና ኢንስቲትዩትና የወለጋ ዩኒቨርሲቲ እገዛ ማድረጋቸዉን ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲያችንም ይህንን ስራ በዋናነት የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሪፌራል ሆስፒታል ኃላፊዎችና ሰራተኞች ሲመሩት ነበር ብለዋል ዶ/ር ታደሰ፡፡ የምዕ/ሸዋ ዞንና የአምቦ ከተማ ጤና ጽ/ቤቶችም የበኩላቸዉን እገዛ ሲያደርጉ እንደነበር ተናግረዉ፣ ሁሉንም ድጋፍ ያደረጉትንና ስራዉን በባለቤትነት የሰሩትን አመስግነዋል፡፡
አምቦ ዩኒቨርሲቲ በጤና ዘርፍ በሚሰሩ ስራዎች ቀድሞ በመተግበር ይታወቃል ያሉት ደግሞ የኢፌዲሪ ጤና ሚ/ር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ሲሆኑ ለዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታደሰ ቀነዓ እና አብሮአቸዉ ለሚሰሩ ለሌሎች የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በጤናዉ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሙያዎችና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ 100 ቀናት መሙላቱን ያስታወሱት ዶ/ር ደረጀ፣ በመከላከሉና በህክምናዉ ላይ በአካባቢዉ የሚሰሩ ስራዎች እንዲጠናከሩ ተከታታይ እገዛና ክትትል እንደሚደረግም አስታዉቀዋል፡፡

የኦርሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንግስቱ በቀለ በበኩላቸዉ ኮቪድ 19 በአገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ወደ ህብረተሰቡ በመሄድ ግንዛቤ በመፍጠር እና አቅመ-ደካሞችን በመደገፍ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ጉልህ ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኦሮሚያ አስከሁን 277 ሰዎች በኮቢድ 19 የተያዙ መሆናቸዉን የተናገሩት ዶ/ር መንግስቱ፣ ይህም ስርጭቱ ወደ ህ/ሰቡ በሰፊዉ መግባቱን አመላካች መሆኑን በመግለጽ ጥንቃቄ የየዕለት ተግባራችን መሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የኮቪድ 1 9 መመርመሪያ ላብራቶሪ እንደ ኦሮሚያ ዛሬ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስራ የጀመረዉን ጨምሮ ቁጥሩ 10 መድረሱንም ዶ/ር መንግስቱ አስታዉቀዋል፡፡
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳህሉ ድርብሳ በበኩላቸዉ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በምዕራብ ሸዋ ዞንና በአምቦ ከተማ በሽታዉን በመከላከልና ህብረተሰቡን በመደገፍ ላሳየዉ ወገናዊ ተሳትፎ አመስግነዉ፣ አዋቂ /ምሁር የሚፈለገዉ ለጭንቅ ቀን ነዉና አምቦ ዩኒቨርሲቲ ይህን በተግባር ፈጽሞታል በማለት በከተማዉ አስተዳደር፣ በምዕራብ ሸዋና በአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ስም ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያም በዩኒቨርሲቲዉ የፋርማሲ ት/ክፍል ዓለም አቀፍ ደረጃዉን ጠብቆ የተመረተዉ ሳኒታይዘር ለእንግዶቹና ለሌሎችም ተሳታፊዎች የታደለ ሲሆን፣ በመቀጠልም በዩኒቨርሲቲዉ ግቢ የችግኝ ተከላ ተካሂዶ የዩኒቨርሲቲዉ ሪፌራል ሆስፒታልና የጉደር ሆስፒታል የኮሮና መታከሚያ ማዕከል በቅደም ተከተል በእንግዶቹ ተጎብኝተዋል፡፡

Modified By: Ambo University, 2020-06-26

Back to News List